በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፥
ብለን ጀመርን
ውዳሴ ኒቆዲሞስ።
በምእራፍ ሦስት
ዘወንጌለ ዮሐንስ፥
ይነበባል
የነገሩ ሁሉ ጥንስስ።
ሌትን ተገን
ያደረገ ‘ማይሄድ በቀን፥
“ወይ መምህር፥
ለካ ኖሯል የሚማር”
የሚለውን
ፈርቶ የአይሁድን ዲስኩር፥
መልአኮሙ
መጽአ ሌሊተ ቀዲሙ።
በጨለማ
ተሸክሞ ኦሪት ጨለማ፥
ብርሃን ወንጌል
ከብርሃነ ዓለም ሊሰማ።
“ሰው ዳግመኛ
ከውሃና ከመንፈስ፥
ሳይወለድ
አይችል መንግሥቱን ሊወርስ።”
ቢለው ጌታ
ቸር መምህር ክርስቶስ፥
ረቀቀበት
እስኪጠራጠር ድረስ።
ብልየቱ
የተጫነው ያ ኦሪቱ፥
“ወደ ማኅፀን
መግባት ነው ወይ ወደ እናቱ?
ብሎ ቢለው
አስረዳው ከመሠረቱ።
ግን ቆይቶ
በጣይ በጉባይ ጠበቃ
ለየኔታው
ለሸንጎ ማስመስከር በቃ።
ስለ ውለታው፥
በዚያች የቁርጧ ሰዓት፥
ልጇን በክብር
አጥቦ የገነዘላትን።
“ታላቅ ያ’ርግህ”
ብላ የአምላክ እናት፥
መረቀችው
እንዲል ርቱዐ ሃይማኖት።
ተገለጠ
የክርስትናው እድገት፥
ዕለት በዕለት
እያደገ በጥቂት።
ከፍርሐት
ወደ ምስክርነት፥
ፍጻሜውም
ከቅዱስ ሥጋው ግንዘት።
መቅበር ሆነ
ብሎ የኪዳን ጸሎት፥
“ቅዱስ ኃያል
ሕያው ዘኢይመውት።
ለታላቅ ሰው
ከታላቁ ጾም ሳምንት፥
ሰባተኛው
ቅድመ ሰሙነ ሕማማት።
ተውህቦ
በያሬድ ሊቀ መጻሕፍት።
ባስተማረው
የተወለድን በጥምቀት፥
ከመቃብር
ያደረው በእጁ ግንዘት።
ይቅር ብሎን
በኒቆዲሞስ ጸሎት፥
በምጽአት
ያሳየን የእርሱን መንግሥት።
ለእግዚአብሔር
ይደሉ ክብር ወስብሐት፥
ለዓለም
ለዘለዓለም እም ጥንት።